Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, October 5, 2016

የእሬቻ ክብረ በዓል ተሣታፊዎችን ፍጅት በተመለከት ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) እና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

የእሬቻ ክብረ በዓል ተሣታፊዎችን ፍጅት በተመለከት ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) እና ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ
============================
የሃያ-አምስት ዓመታት የሕወሐት አገዛዝ ቁም ስቅላችሁን ያሣያችሁና ከመሞት በላይ ከመኖር በታች የሆነ የሰቀቀን ኑሮ የምትገፉ ዉድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሆይ፡-

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) እና የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከቡሾፍቱ የተሠራጨዉን የወገኖቻችንን እልቂት የሚገልፅ እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነ ዜና የተከታተልነዉ በቃላት ለመግለፅ በሚያስቸግር የሃዘንና የጭንቀት ስሜት ነዉ፡፡

የፋሺስቱ ወያኔ አጋዚ ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ቡሾፍቱ በሚገኘዉ ሆረ አርሰዲ የእሬቻን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የወሰደዉ ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ህዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ በመንግሥትነት ሥልጣን ላይ በተቀመጠ አካል ዕዉቅናና ትዕዛዝ የተፈፀመ መሆኑ የዚህን ዘረኛ ሥርዓት መሪዎች እንደሰዉ ማሰብ መቻል እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ የእሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ታግሎና ተንከባክቦ በመጠበቅ ካቆያቸዉ የማንነቱ መገለጫ ከሆኑት እሴቶቹ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንደተገለፀዉ በአገራችን ታሪክ እስከዛሬ ታይቶና ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ባህላዊ እምነታቸዉን በሚያከብሩበት ሥፍራ በጣም ብዙ ዜጎቻችን በአጋዚ ነፍሰ ገዳዮች ወደ ገደል ተነድተዉና በጥይትም ተጨፍጭፈዉ አልቀዋል፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የበዓሉ ተሣታፊዎች ደግሞ ይህ መግለጫ እስከሚዘጋጅበት ጊዜ ድረስ የደረሱበት አለመታወቁን ከሥፍራዉ ከተላለፉልን መረጃዎች ለማወቅ ችለናል፡፡ ይህን የሕወሐት ድርጊት የበለጠ አሣዛኝና እጅግ በጣም ዘግናኝ የሚያደርገዉ ደግሞ የእነዚህ ዜጎች ወንጀል በሕወሐት አረመኔያዊ አገዛዝ ሥር ታፍነን መማቀቅ በቃን ብለዉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃዉሟቸዉን ለመግለፅ መሞከራቸዉ ብቻ የመሆኑ እዉነታ ነዉ፡፡

ይህ የጭካኔ እርምጃ የሕወሐት/ኢህአዴግ አገዛዝ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለዉ ንቀትና ጥላቻ መሠረት በማን አለብኝነት ፍትሃዊ ጥየቄ ባነሱ የአገራችን ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያወጀዉን ጦርነት ወደመተግበር መሸጋገሩን የሚያሣይ ነዉ፡፡ ስለሆነም ይህን በሰላማዊዉ የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተደረገ ለማመን የሚያስቸግር ግድያ በመግለጫ ብቻ ማዉገዝ በቂ እንዳልሆነ ይሰማናል፡፡ ለደረሰዉ የሰዉ ህይወት ጥፋት ብቸኛ ተጠያቂዉ የሕወሐት/ኢህአዴግ መንግሥት በመሆኑ መሪዎቹ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ልናሰምርበት እንወዳለን፡፡ ይህን ዓይነት ዘግናኝ እልቂት ለማስቀረት የሚቻለዉ የሕወሐት/ኢህአዴግን አገዛዝ በማስወገድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህን አገዛዝ ለማስወገድ ደግሞ በተቃዉሞዉ ጎራ ያለን ኃይሎች አንድ ላይ ሆነን ለነፃነት የሚደረገዉን ትግል የበለጠ ማፋፋም ብሎም ጠንካራ አማራጭ ኃይል ሆነን በመገኘት በህዝባችን እየተካሄደ ያለዉን ትግል ከግብ ማድረስ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ረገድ ኦዲግ እና አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በጋራ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምረናል፡፡ ይህ አሁን የደረሰዉ ዕልቂት ደግሞ የጀመርነዉን የጋራ ትግል የበለጠ አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያደርገን መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

የተከበራችሁ ወገኖቻችን ሆይ፡-

የአሁኑ መስዋዕትነታችሁ በሕወሐት የሚመራዉን ሥርዓት በተቀናጀ መልኩ ታግለን ለመጣል የጀመርነዉን የጋራ ትግል በአስቸኳይ ወደ ሰፊ የአንድነት፣ የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ታገዮች ህብረት በማሸጋገር ይህን የወንበዴዎች ቡድን በማስወገድ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነበትን ሥርዓት በአገራችን ዕዉን ለማድረግ የበለጠ ተግተን እንድንሠራ ያስገድደናል፡፡ ስለሆነም እስከዛሬ በሕይወትና በአካል የከፈላችሁትና እየከፈላችሁ ያላችሁት መስዋዕትነት ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡ በዚህም ላይ ተመሥርተን የወያኔ የግፍ ድርጊቶች ገፈት ቀማሽ ለሆናችሁት ሕዝቦቻችንና በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ ላሉ የኢትዮጵያ የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ታጋዮች የሚከተለዉን ጥሪ ስናቀርብ ሁላችሁም የአሁኑ የሕወሐት አረመኔያዊ ድርጊት ከምን ጊዜዉም የተለየ መሆኑንና በሥርዓቱ ቁንጮዎች የታወጀብንን ግልፅ ጦርነት በቀላሉ የማንመለከተዉ መሆኑን ተረድታችሁ የየበኩላችሁን እንደምታደርጉ በመተማመን ነዉ፡፡

1. ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በሙሉ፡-

የሕወሐት/ኢህአዴግ መሪዎች ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት አንተን ከሰዉነት ዉጭ አድርገዉ ለአስከፊ ችግር፣ ለሰቆቃ፣ ለስደትና ለመፈናቀል ዳርገዉህ እነርሱ ግን ያንተኑ አንጡራ ሃብት በተለያየ መንገድ በመዝረፍ ቅንጦት የተመላበት ኑሮ መኖር አልበቃ ብሏቸዉ ዛሬ ደግሞ ያወጁብህን ጦርነት በግልፅ መተግበር ጀምረዋል፡፡ ባለፉት 11 ወራት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በኮንሶ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ያለምንም ጥፋት በግፍ መገደላቸዉ ይታወሳል፡፡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዉድ ልጆችህን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ዉስጥ እንደፋብሪካ አስፋፍተዉ በከፈቷቸዉ የማሰቃያ ማዕከላት ዉስጥ አጉረዉ በታሪክ ከምናዉቀዉ በናዚ ማጎሪያ ቤቶች ይደረግ ከነበረዉ የማሰቃያ መንገድ በከፋ ሁኔታ ከማሰቃየትም አልፈዉ እሥር ቤቶችን በእሳት በማጋየት ሰዉን ያህል ክቡር ፍጡር አቃጥለዉ ሲገድሉ ታዝበናል፡፡ እነርሱ በሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጃቸዉ እንዳለ ሆኖ አንተ ያነሣህባቸዉን የአልገዛም ባይነት ሰላማዊ የተቃዉሞ ጥያቄ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠርከዉ በማስመሰል የሕዝብ-ለሕዝብ ፍጅት ለማስነሣት የዉሸት ፕሮፓጋንዳ በሰፊዉ ነዝተዋል፡፡ መስከረም 22 ቀን 2009 ቡሾፍቱ በሚገኘዉ ሆረ አርሰዲ ዓመታዊዉን የእሬቻ በዓል ለማክበር በተሰበሰበዉ የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፈፀሙት የግፍ ጭፍጨፋ ያወጁብህን ጦርነት ወደከፍተኛ ደረጃ እያሸጋገሩት መሆናቸዉን በገሃድ የሚያሣይ ነዉ፡፡ የሕወሐት/ኢህአዴግ መሪዎች ይህን እርምጃ የወሰዱት የአንተ በልበ-ሙሉነት የአልገዘም ባይነት ትግልህን አጠናክረህ መቀጠል ተስፋ አሰቆርጧቸዉ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ይህ የቡሾፍቱ ጭፍጨፋ በቀላሉ ከታለፈ እነዚህ ተስፋ የቆረጡ የወያኔ መሪዎች ተመሣሣይ ጭፍጨፋዎችን በሌላዉም ሕዝብ ላይ የማይደግሙበትና አንተን ፀጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት የሚያስችላቸዉን እርምጃ አጠናክረዉ የማይቀጥሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለሆነም የእኔ ነዉ ብለህ የምትቀበለዉን በነፃነት፣ በዲሞክራሲ፣ በፍትህ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መንግሥት እስክታቋቁም ድረስ የጀመርከዉን ሰላማዊ የተቃዉሞ ትግል ለአፍታ እንኳን ሳታቋርጥ እርስ በእርስህ ተባብረህና ተረዳድተህ የበለጠ አጠናክረህ ቀጥል እያልን ጥሪ ስናቀርብልህ ምንጊዜም ከጎንህ መሆናችንን እያረጋገጥን ነዉ፡፡

2. በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ በመንቀሳቀስ ላይ ለሆናችሁ የወያኔ ተቃዋሚ ኃይሎች በሙሉ፡-

ከመቼዉም ጊዜ በላይ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የእኛን የተባበረ ኃይልና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ አብረን መቆም ከሚፈልጉበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥማት ከሁሉም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶቻችን አስበልጠን ማየት ይኖርብናል፡፡ አገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታና በሕዝባችን ላይ እየተፈፀሙ ያሉት የግፍ ድርጊቶች እልባት ካላገኘንላቸዉ እንታገልለታለን የምንለዉ ሕዝብ ህልዉናም ሆነ ከወያኔ ነፃ እናደርጋታለን የምንላት የጋራ አገራችን እንደ አገር መቀጠል ጥያቄ ዉስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተዉ ለትልቁ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተን የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ጊዜ የማይሰጠዉ ጉዳይ መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን፡፡ ስለዚህ እንደ የፖለቲካ ኃይሎች ተደራጅተን የምንንቀሳቀስ ወገኖች ሁሉ ሕወሐት የከለለልንን “በአገር ዉስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ” እና “ከአገር ዉጭ ያሉ” ወይም “ህጋዊ የሆኑ እና ያልሆኑ” የሚለዉን የሕወሐት ከፋፋይ ሴራ ወደጎን ትተን ተቀራርበን በመሥራት ይህን ፈታኝ ወቅት ማለፍ የማንችል ከሆነ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከመሆን የማንድን መሆኑን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለሆነም በአንድነት መንፈስ እየተዋደቀ ያለዉ ሕዝባችን ከምንም በላይ የሚፈልገዉንና በተለያዩ መንገዶች እየጠየቀ ያለዉን የተማከለ የፖለቲካ አመራር መስጠት የሚያስችለንን ሰፊ መሠረት ያለዉ ትብብር ለመመሥረት የጀመርነዉን ጉዞ እንድናፋጥንና ወደ የጋራ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንድንገባ ልባዊ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርብላችኋለን፡፡

ፍትህና ነፃነት ለሁሉም ሕዝቦች!!

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) እና የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ
መስከረም 2009 ዓ. ም.
http://www.patriotg7.org/?p=1085

No comments:

Post a Comment

wanted officials