Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, August 6, 2017

በባህርዳር ከ50 በላይ ወጣቶች የተጨፈጨፉበትን ቀን ለማሰብ ከቤት ያለመውጣት አድማ ተጠራ

በባህርዳር ከ50 በላይ ወጣቶች የተጨፈጨፉበትን ቀን ለማሰብ ከቤት ያለመውጣት አድማ ተጠራ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 28/2009) በአንድ ቀን ብቻ በህወሃት አጋዚያን ከ50 በላይ ወጣቶች የተጨፈጨፉበትን ቀን በሀዘን ለማስታወስ በባህር ዳር ነሐሴ 1/2009 ከቤት ያለመውጣት አድማ ተጠራ።
የወጣቶቹን 1ኛ አመት ጅምላ ግድያ በሀዘን ለማስታወስ ከቤት ያለመውጣት አድማውን ለሰኞ የጠራው የባህርዳር ወጣቶች አስተባባሪ ኮሚቴ በሚል በህቡእ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው።
በሕወሃት አጋዝያን ጭካኔ ኮብል በተባለ አካባቢ በአንድ ስፍራና ሰአት የተረፈረፉትን ወጣቶች ለማስታወስ የጎንደር ከተማ ህዝብም ከቤት ባለመውጣት የሐዘኑ ተካፋይ እንዲሆን ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።
ባለፈው አመት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል በወልቃይት የማንነት ጥያቄ መነሻነት መላው የባህርዳር ሕዝብ በደባባይ በመውጣት ያስተጋባው ሰላማዊ ጥያቄ ምላሹ በጥይት መደብደብ ነበር። የጎንደር ከተማ ህዝብ በቀነኒሳ ወይም የተቃውሞ ችቦውን ከለኮሰ በኋላ ባህርዳሮችም አጋርነታቸውን ወዲያውኑ ነበር ያሳዩት። የአማራ ህዝብ የመብት ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑንም አሳይተዋል። እንኳን የወልቃይት እንኳን የጎንደርና የአከባቢው ነዋሪ የኦሮሞ ህዝብ ደምም ደሜ ነው ሲሉም ነበር። መስዋእትነት የከፈሉት ነሃሴ 1/2008 አ ም ያለፈው አመት የመብት ጥያቄን በሰላማዊ ሰልፍ በነቂስ ወጥተው ያስተጋቡ ወጣቶች በጅምላ ተረፍርፈዋል። በጅምላ ታስረው መከራና ስቃይን ተቀብለዋል።
የባህርዳር ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አደባባዩን በመሙላት አገዛዙን በሰላም ሲያወግዝ ውሏል። ሰላም የማይወደው የህውሃት አገዛዝ ግን አባይ ማዶ ኮብል በተባለ ቦታ በኮንዶሚኒየም ቤት ላይ ቀድሞ እንዲያደፍጡ ቢያደርጋቸውም አነጣጥሮ አልሞ ተኳሾች በአንድ ስሜት ውስጥ ብቻ ከ50 በላይ ወጣቶች ተረፍርፈዋል። እነዚህን ወጣቶች የገደሉት የአገዛዙ ታጣቂዎች ግን አንዳቸውም እስካሁን ላይረዱ አልቀረቡም። ይልቁንስ ሰላማዊ ተቃውሞ ያነሱ ከ15ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በብርሸለቆ ማጎሪያ ተጋዘው ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፤ አይደገምም በሚልም በግዴታ እንዲምሉ ተደርገዋል። አሁንም እስር ቤት የሚገኙ በርካታ ናቸው። እነዚያ በግፍ የወደቁ 50ወጣቶች ደማቸው በከንቱ ፈሶ አይቀርም ይላሉ የብህር ዳር ወጣቶች። ወንድምና እህቶቻችን አንረሳቸውም ሲሉ ለከተማዋ ህዝብ ቀኑን በሃዘን ለማሰብ ከቤት ያለመውጣት አድማ ከሰኞ ነሐሴ 1/2009 አ ም ይፋዊ ጥሪ አድርገዋል። በዚሁ አድማም የንግድ መደብሮች እንዲዘጉ፣ በጎዳና ላይ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግና በከተማዋ ጸጥታ በማስፈን ፍጹም የሆነ ሐዘናችንን በሰላማዊ መንገድ እንገልጻለን ብለዋል። ወጣጦችና ልጆቻቸው የተጨፈጨፉባቸው ወላጆችም የሐዘን ካባ ለብሰው አይቀሩም ለነጻነት የሚደረገው ትግል ይቀጥላል ነው ያሉት ወጣቶቹ። እናም ይህን ጥሪ ለመላው ህዝብ አድርሱልን ሲሉ የባህርዳር ወጣቶች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለኢሳት በላኩት መግለጫ አመልክተዋል። የጎንደር ህዝብም ሆነ የአከባቢው ህብረተሰብ ከቤት ባለመውጣት በአድማው ባለመሳተፍ በባህርዳር ለተገደሉ 50 ወጣቶች ሃዘኑን በመግለጥ እንዲተባበር ጥሪ አድርገዋል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ጨምሮ የኦሮሞ ማህብረሰብ ለነጻነቱና ለመብቱ በጋራ የሚያደርገውን ትግል እንደሚደግፍም ገልጸዋል። በአንድ ሰአት፣ በአንድ ቦታ፣ ቀድመው ባደፈጡ አጋዚያን አልሞ ተኳሾች 50 ወጣቶች በአንድ ጊዜ የተፈረጀበት ቀን ነሐሴ 1/2008 አ የባህር ዳር ወጣቶች ሰማእታት ቀን።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በባህርዳር ከተማ የንግድ ተቋማትን ለማዝጋት ጥረት ሲያደርጉ ነበር የተባሉ 5 ግለሰቦች መያዛቸውን የከተማዋ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ገልጿል።
የከተማዋ የጸጥታ መዋቅር 5 ግለሰቦችን ይዟል ቢባልም የተያዙት ሰዎች ማንነት ስምና አድራሻ ባለመገለጹ ሆን ተብሎ ሰኞ ነሐሴ 1 በግፍ የተጋደሉትን የባህርዳር 50 ወጣቶች ለማስታወስ የተጠራውን አድማ በማስፈራራት ጥሪውን ለማኮላሸት የተቀናበረ ዜና መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመዋል።
አምስቱ ወጣቶች ከተያዙ በኋላ በተመሳሳይ የተሰማሩትን ግለሰቦች መረጃ ሰምተዋል በሚልም የህዝቡን ቤት ለመዋል የተጠራ አድማ በማስፈራራት ለማስቀረት አገዛዙ እየተፍጨረጨረ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በባህርዳር ከተማ የሚገኙ አባላቱን የትግራይ ልማት ማህበር ጠርቶ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አድማውን ለማስቀረት የመረጃ ስራ እንዲሰሩ በስብሰባ ተነግሯቸዋል።
ነሐሴ 1/2008 ባለፈው አመት በባህርዳር ከተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ በአንድ ስሜት ውስጥ የተገደሉትን 50 ወጣቶች ለማስታወስ ኢሳት ከግድያው ጀርባ የነበረውን ስራ የሚያጋልጥ ሪፖርታዥ የሚያቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።

No comments:

Post a Comment

wanted officials