Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, August 10, 2017

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ህዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱ ተሰማ

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ህዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሷል። በሰሜን ጎንደር በመተማ፡ በአይከል፡ አርባያ፡ በበለሳ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ወደ ደብረማርቆስ የሚወስደው መንገድ በህዝቡ ተዘግቷል።
በምስራቅ ሀረርጌ በባቢሌ መስመር የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሷል።በርካታ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
በወልቃይት አዲረመጽ የህወሃት ታጣቂዎች ገብተው ህዝቡን እያሸበሩት መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በወሊሶና ጊንጪ አድማው እንደቀጠለ ነው። በሀዋሳ በባጃጅ አሽከርካሪዎች ትላንት የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ቀጥሏል።
በሰሜን ጎንደር በበርካታ አካባቢዎች አድማ ተጀምሯል።
በመተማ ወረዳ በመተማና ኮኪት ከተማ ወደ ህዝባዊ አመጽ የተሸጋገረ አድማ መጀመሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ከጎንደር ወደ ሱዳን በሚወስደው ዋናው መንገድ ላይ ባሉ ከተሞች አድማው ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች የተኩስ ድምጽ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
በጭልጋ አይከል፡ ነጋዴ ባህር፡ አይምባ በተባሉ ከተሞች የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል። በበለሳ ወረዳ አርባያ ከተማም ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው አድማውን ተቀላቅለዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ከደብረ ማርቆስ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በግምት 25 ኪ.ሜ ረዕቡ ገበያ የሚባል ስፍራ የሚወስደው መንገድ ሙሉ በሙሉ በህዝቡ ተዘግቷል። ብዛት ያለው የልዩ ሃይል እና መከላከያ በአካባቢው ሰፍሯል። ከረዕቡ ገበያ ወደ ደብረ ማርቆስ ምንም አይነት የትራንስፓርት እንቅስቃሴ የለም።
በባቢሌ መስመር ቆሬ እየተባለ በሚጠራው ቦታ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሊያ ልዩ ሃይል ጋር ትንቅንቅ ውስጥ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመለከተ። ህዝቡ ባለው መሳሪያ ከልዩ ሃይሎች ጋር እየተዋጋ ነው።
የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንዲሁም በፉኛን ቢራና ጉርሱም ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ ተካሂዷል። ትላንት የአሜሪካን መንግስት በሀረርና በባቢሌ መሃል ያለው መንገድ በመዘጋቱ ዜጎቹ ከእንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፉ ይታወሳል። ዛሬ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ የአሜሪካን መንግስትን መረጃ አጣጥለዋል። በተጠቀሰው አካባቢ የተዘጋ መንገድም ሆነ የተደረገ የተኩስ ልውውጥ የለም ብለዋል-ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ።
በግብር ተመኑ የተነሳ ተቃውሞ በጀመሩ የኦሮሚያ ከተሞች አሁንም አድማው እንደቀጠለ ነው። በወሊሶና ጊንጪ ዛሬም አብዛኞቹ የንግድ ቦታዎች ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነው ውለዋል። በአምቦም ተመሳሳይ የአድማ እንቅስቃሴ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማል።
በባህርዳር በነጋዴዎችና ባለሀብቶች ላይ የተጀመረው የእስር ዘመቻ የቀጠለሲሆን፡ ዛሬ ከ150 በላይ የሚሆኑ ታስረው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል። በደብረታቦር ዛሬም አድማ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። በምዕራብ ጎጃም ደምበጫም እንዲሁ ለተከታታይ ቀናት ሱቆችና መደብሮች ተዘግተዋል።
ሀዋሳ ትላንት የተጀመረው የባጃጅ አሽከርካሪዎች የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ቀጥሏል። በአስፓልት መንገዶች ላይ አገልግሎት እንዲያቆሙ በመደረጋቸው የተቃወሙት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በትላንትናው ዕለት ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውንና የመንግስት ተሽከርካሪዎችን ማጥቃታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ዛሬ ጥያቄ ይዘው ወደሚመለከተው አካል ቢሄዱም ተቀባይነት አላገኙም። በአድማው ቀጥለዋል። በሌላ በኩል በሀዋሳ አዲሱ ገበያ ዛሬ ሌሊቱን ከ20 በላይ ሱቆች በግሬደር መፍረሳቸውን ተከትሎ በአከባቢው መለስተኛ ውጥረት መፈጠሩ ተገልጿል።
ወደ ገበያው የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ እንደነበርና ሱቃቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ተቃውሞ እያሰሙ መሆኑንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል የህወሀት ወታደሮች ወደ ወልቃይት አዲረመጽ ከተማ በብዛት መግባታቸውን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ገልጸዋል። የአመጽ ጥሪ ተደርጓል በሚል ወደ ከተማዋ የገቡት ወታደሮች ነዋሪውን እያሸበሩት እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በከተማዋ መግቢያና መውጪያ ያሉ ኬላዎች በወታደሮቹ ተከበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በበለሳ የአርበኞች ግንቦት7 ንቅናቄ ታጣቂዎች ከስርዓቱ ወታደሮች ጋር መዋጋታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በበለሳ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆላ ሀሙሲት ላይ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በመንግስት ወታደሮች ላይ የሞትና የመቁስል አደጋ የደረሰ መሆኑን ንቅናቄው ከላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። ኢሳት ንቅናቄው አደረኩ ስላለው ጥቃት ከመንግስት በኩል ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials