Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, August 17, 2017

ሕወሃት የአፓርታይድ ስርአትን በኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገ ነው ተባለ


ESAT
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣኑን የያዘው የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ/ሕወሃት/ቡድን የአፓርታይድ ስርአትን በመገልበጥና በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያውያንን እየጨቆነና እየመዘበረ መሆኑን አንድ አሜሪካዊ የሕዝባዊ ንቅናቄ ኤክስፐርት ገለጹ።
አሜሪካዊው ኢኮኖሚስትና የህዝባዊ ንቅናቄ ኤክስፐርት ዴቪድ ስቴማን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ የአፓርታይድ ስርአት በሚገባ ተጠንቶ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ብዙሃኑ እየተገፋ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካዊው ኢኮኖሚስትና የህዝባዊ ንቅናቄ ኤክስፐርት ዴቪድ ስቴማን ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አናሳዎች የፖለቲካ ስልጣን ሲይዙ የብዙሃኑን ሀብት በመበዝበዝ ስራ ላይ ይጠመዳሉ ሲሉ ነው የተናገሩት።
በዚህ ረገድ የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ ስርአት ከኢትዮጵያው የሕወሃት አገዛዝ ጋር በማነጻጸርም ተመልክተውታል።በደቡብ አፍሪካ የነጮች የአናሳ አገዛዝ ከብዙሃኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ላይ የሚፈጽመውን ዘረፋ ፍትሃዊ ተግባር እንደሆነ ለማሳየት ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያ ሲደገም መታየቱ የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም ያሉት አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ዴቪድ ስቲማን የአፓርታይድ ስርአት በሚገባ ተጠንቶ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ብዙሃኑ እየተገፋ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ እየታየ ነው በሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ጥያቄ ያነሱትና ይልቁንም የሀገሪቱ መሪዎች በዘረፋ ላይ መጠመዳቸውን ያወሱት ኢኮኖሚስቱ ዴቪድ ስቴማን የኢኮኖሚ እድገት ከፖለቲካ ምህዳሩ ጤናማነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሰብአዊ መብት በማይከበርበትና የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት እንደማይኖር ተናግረዋል።
የሕወሃት ሰዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት መጨረሻው አስከፊ እንደሚሆንም አሳስበዋል።
ለዚህ ችግር ግንባር ቀደሙ ተጣያቂ ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዲሞክራሲና የህግ የበላይነትን አሰፍናለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ዘራፊና ጨቋኝ ስርአት ጥሎ ሔዷል በማለት መለስ ዜናዊን ተጠያቂ አድርገዋል።
ታማኝ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ በማድረግም የሀገሪቱ መሪዎች ወደ 30 ቢሊየን ዶላር መዝረፋቸውን የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሀብት ደግሞ 3 ቢሊየን ዶላር መድረሱን አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ገልጸዋል።
ሴሌብሪቲ ኔት ዎርዝ የአቶ መለስ ዜናዊ ሀብት 3 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ሲገልጽም የተጠኑ የምርመራ ዘዴዎችንና የታመኑ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials